በውልደት ምጣኔ የስነ ህዝብ ቀውስ ያጋጠማቸው ሀገራት የወታደር መመልመያ እድሜን እያሻሻሉ ነው፡፡ በ2022 እስከ 50ሺህ አዳዲስ ወታደሮችን ለመመልመል አቅዳ የነበረችው ጃፓን 4ሺህ ምልምሎችን ብቻ መዝግባለች፡፡

በውልደት ምጣኔ መቀነስ በስነ ህዝብ ቀውስ ውስጥ የሚገኙት የእስያ ሀገራት በመጪዎቹ አመታት ወታደራዊ አቅማቸው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡

 ቻይና ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮርያን የመሳሰሉ ሀገራት ዜጎቻቸው ልጆችን እንዲወልዱ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እየሰጡ ነው፡፡

ሀገራቱ የውልደት ምጣኔያቸው ሲቀንስ በአንጻሩ በከፍተኛ ደረጃ እየተወነጨፈ የሚገኝው በእድሜ የገፉ ዜጎቻቸቸው ቁጥር ለስነ ህዝብ ፖሊሲያቸው ስጋትን ደቅኗል፡፡

የውልደት መጠን መቀነስ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ የሚፈጥረውን ቀውስ ለማስቀረት የተለያየ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ የሚገኙት ሀገራት፣ በወታደራዊ የሰው ሀይላቸውም ላይ ሊያስቡበት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

የሰላም እና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች ተመራማሪዎች በእነዚህ የእስያ ሀገራት ያለው የስነህዝብ ቀውስ የወታደሮቻቸው ቁጥር እንዲቀንስ በማድረግ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ 

የ18 ወራት ብሔራዊ ውትድርናን በአስገዳጅነት ተግባራዊ የምታደርገው ደቡብ ኮርያ በአሁኑ ወቅት 500 ሺህ ወታደር ቢኖራትም ይህን ቁጥር ለማስቀጠል አዳዲስ ቋሚ ወታደሮችን መመልመል ይጠበቅባታል፡፡

በመጪዎቹ አመታት በጡረታ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከጦሯ የሚወጡ ወታደሮችን ለመተካት የወጣቶቿ ቁጥር አናሳ መሆን እክል ይሆንባታል፡፡ የወጣቶቿ ቁጥር ማሽቆልቆል በዚህ ከቀጠለም የወታደሮችን የአገልግሎት ዘመን በማሳጠር በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲሰማሩ ልታደርግ ትችላለች፡፡ 

በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ወታደራዊ ምልመላ የምታካሂደው ጃፓን ባለፉት 10 በላይ አመታት የበጎ ፈቃደኛ ምልምል ወታደሮች ቁጥር በ30 በመቶ ቀንሶባታል፡፡ በ2022 የሀገሪቱን ጦር በፈቃደኝነት የተቀላቀሉ ጃፓናዊያን ቁጥር 4ሺህ ብቻ ነው፡፡

በዚህ የተነሳም ጃፓን የምልምል ወታደሮችን የመመዝገቢያ እድሜ ከ26 ወደ 32 ከፍ አድርጋለች፡፡ 

ቻይና በበኩሏ በመጪዎቹ አመታት ሊያጋጥማት የሚችለውን የወታደር ቁጥር መቀነስ ለመከላከል ቁመት እና ክብደትን የመሳሰሉ የመመልመያ መስፈርቶችን አሻሽላለች፡፡  

በአለም ላይ ከሚጠቀሱ ግዙፍ ጦሮች መካከከል አንዱ የሆነውን መከላከያ የምታዘው ቻይና የስነ ህዝብ ፖሊስ በወታደራዊ አቅሟ ላይ ከሚፈጥረው ተጽእኖ ይልቅ ኢኮኖሚዋ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከቻይና በእጅጉ ያነሰ የህዝብ ቁጥር ባላቸው ደቡብ ኮርያ እና ጃፓን ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ 

ኒውስዊክ ጋዜጣ ያነጋገራቸው የአለም አቀፍ ጉዳዮች አጥኚው ፕሮፌሰር አንድሪው ኦሮስ የስነ ህዝብ ቀውስ በወታደራዊ አቅም መዳከም ላይ የማይካድ ተጽእኖ ቢኖረውም፣ ሀገራቱ ከሚገኙበት ኢኮኖሚያዊ አቅም አንጻር የሰው ሀይል ክፍተታቸውን በቴክኖሎጂ ሊሞሉት እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡  

በምንገኝበት ግዜ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች የሚገኙበት መራቀቅ የሰው ልጅን የጦር ሜዳ ተሳትፎ የሚቀንሱ ናቸው ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

ሆኖም አንዳንድ ቴክኖሎጂዎችን ለማንቀሳቀስ ሰዎችን መጠየቃቸው ቴክኖሎጂ ለችግሩ መቃለል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

By Al Ain Amharic News

አል ዐይን ኒውስ ሁሉን አቀፍ ሽፋን የሚሰጥ እና የዓለም ክስተቶችን በወቅቱና በጊዜው ለተከታዮቹ ያቀርባል፡፡

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው