ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት የወጣው ዜና በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ግንኙነት ላይ ትልቅ ለውጥ ያስከተለ ነበር። ምን አልባት በሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪክ ውስጥ በጉልህ ከሚጠቀሱት ሊሆን ይችላል።

ዜናው፣ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ግዛቴ ከምትላት እና ራሷን ነጻ አገር ብላ ከወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለመጠቀም የሚያሰችላትን የመግባቢያ ሰነድ ፈረመች የሚል ነው።

ሶማሊያን በእጅጉ ያስቆጣው ይህ ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በሶማሊያ በኩል በአካባቢው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን የሚያስከትሉ በርካታ ነገሮች ተሰምተዋል።

ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በርካታ የሶማሊያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሰምምነቱን “ጦርነት ከማወጅ” ጋር የሚስተካከል ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ኢትዮጵያን የአገራቸው “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት ነች” ሲሉ በይፋ ከሰዋታል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ሉአላዊነቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አረብ ሊግ ድረስ በመውሰድ ድጋፍ ለማግኘት ሞክራለች።

ከስምምነቱ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ድጋፍ ለማሰባሰብ በኤርትራ ካደረጉት ሁለት ጉብኝቶች በተጨማሪ፣ ወደ ግብፅ እና ወደ ሌሎች የአረብ አገራት ተጉዘው ነበር። እንዲሁም ከቱርክ ጋር አነጋጋሪ የሆነ ወታደራዊ ስምምነት ፈርመዋል።

የሁለቱ አገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማቋረጥም በሞቃዲሾ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ስታስወጣ፣ ሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ወስና ነበር።

ሰሞኑን ደግሞ ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ስር በሰላም አስካባሪነት በአገሪቱ ለዓመታት ተሰማርተው የሚገኙ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከሶማሊያ እንዲወጡ እንደምትፈልግ ገልጻለች።

ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ

በሶማሊያ ሲደረግ የነበረው የእስር በርስ ጦርነት ተፋፍሞ ታላቋ ሶማሊያን ለመፍጠር ህልም የነበረው የሲያድ ባሬ አስተዳደር በ1983 ዓ.ም. ሲገረሰስ ሶማሊያም እንደ አገር የመፍረስ ዕጣ ገጠማት። ይህ ነበር አሁን ሶማሊያ ላለችበት ምስቅልቅል መነሻ የሆነው።

ከማዕከላዊው መንግሥት መውደቅ በኋላ የበላይነትን ለማግኘት ለዓመታት ከተፋለሙት የሶማሊያ የጦር አበጋዞች መካከል ፈርጥሞ ማዕከላዊ መንግሥቱን መቆጣጠር የሚችል ኃይል አልነበረም። ይህ ሶማሊያን መንግሥታ አልባ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መራት።

የጎሳ እና ሃይማኖታዊ ቡድኖች የበላይነትን ለማግኘት በጦር መሳሪያ ያደረጉት ጥረት ውጤታማ ካለመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ የሶማሊያ አጎራባች አገራት ስጋትም አስከትሏል።

ሶማሊያ እንድትረጋጋ እና መንግሥት እንዲቋቋም ጉልህ ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር በመሆን በአገሪቱ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ለማድረግ ቢቻልም የሚጠበቅበትን ለመከወን ግን አቅም አልነበረውም።

ይልቁንም በሶማሊያ ካሉ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ጠንካራ መሆን ችሎ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ኃይል በርከት ያሉ የአገሪቱን ግዛቶች መቆጣጠር ችሎ ነበር።

በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላትን ሚና አጥብቆ የሚቃወመው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ጡንቻው እየፈረጠመ ሲመጣ ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት የመፈጸም እና ወረራ የመክፈት ዛቻን በተደጋጋሚ ይሰነዝር ጀመረ።

ይህ ሁኔታ ስጋት የፈጠረባት እና ቡድኑም ከፍላጎቷ በተቃራኒ ያላ መሆኑ ያሳሰባት ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ አሰማርታ ኅብረቱን ከያዛቸው የአገሪቱ ግዛቶች ከማስወጣቷ ባሻገር እንዲዳከም አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ወሳኝ እርምጃን ተከትሎም የአፍሪካ ኅብረት ኃይሉን በሶማሊያ በማሰመራት ማዕከላዊ መንግሥቱ እንዲጠናከር ለማድረግ እግሩን ወደ አገሪቱ አስገባ።

ጥር 11/1999 ዓ.ም፣ ከ17 ዓመታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ከተለያዩ አገራት የተወጣጣው ሰላም አስከባሪ ኃይል ለስድስት ወራት በሶማሊያ እንዲቆይ ተሰማራ።

ይህ ከመሆኑ አንድ ዓመት አስቀድሞ በአፍሪካ ኅብረት ይሁንታ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) አማካይነት ሰላም አስከባሪ ተሰማርቶ አስተዳዳሪዎችን መጠበቅ እና የፀጥታ ኃይል የማሠልጠን ሥራን ሲያከናውነ ቆይቷል።

የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት ለማጠናከር እና ሶማሊያን ለማረጋጋት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ አገሪቱ ሲያሰማራ የተባበሩት መንግሥታትን እና የምዕራባውያንን ድጋፍ አግኝቶ ነበር።

በአካባቢው ከፍተኛ ተጽእኖ የነበራት ኢትዮጵያም የዚህ ኃይል አካል ብቻ ሳትሆን ዋነኛ ተዋናይ ነበረች። ነገር ግን ይህ ወደ ሶማሊያ የተደረገው የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪት በአገር ውስጥ ከአንዳንድ ወገኖች ታቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሶማሊያ የሚገኘው የእስላዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ኃይል የኢትዮጵያ ስጋት እንደሆነ እና ስምሪቱም የአጭር ጊዜ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ነገር ግን ለስድስት ወራት ወደ ሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቆይታ አሁን 17 ዓመታትን አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት መውጣት ጥያቄ

ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የጎላ ድርሻ እንዳላት ይነገራል። አንዳንዶች አሚሶም (ሰላም አስከባሪው ኃይል) ለሶማሊያ አንጻራዊ መረጋጋትን አምጥቷል ሲሉ፣ ሌሎች ግን ለአልሸባብ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ።

በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግጭቶች እና የደኅንነት ተንታኙ ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ “የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን እናጠፋለን ብለን ገብተን አልሻባብን ነው የፈጠርነው” ብለው ነበር።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛውን ድርሻ በያዘበት የሰላም አስከባሪ ኃይል በ2001 ዓ.ም ለሁለት ዓመት በነበረው ቆይታ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን በሳምንታት ውስጥ ማፍረስ ችሎ ነበር።

ሆኖም ግን ይህ ድል የበለጠ ሰፍቶ የሶማሊያ መንግሥት ከመጠናከሩ በፊት ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረቱ ፍርስራሽ ላይ ዛሬም ድረስ የምሥራቅ አፍሪካ የሰላም እና የደኅንነት ስጋት የሆነው አልሸባብ የተሰኘው ጽንፈኛ ቡድን ብቅ አለ።

በሶማሊያ የተሰማራው የአገራት ሠራዊት ቆይታው በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት እየተራዘመ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም ሰላም አስከባሪው ሚናውን ለሶማሊያ መንግሥት አስረክቦ ከአገሪቱ እንዲወጣ ቢወሰንም መፍትሄ ያላገኘው የአልሻባብ እንቅስቃሴ ግን አሁንም ስጋት እንደሆነ አለ።

በዚህ የዓመታት ሂደት ውስጥም በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወይም አሚሶም የተሰኘው ዘመቻ ወደ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ ተቀይሮ አሁን ድረስ ዘልቋል።

በአልሻብብ እንቅስቃሴ ምክንያት ሁሉንም የአገሪቱን አካባቢዎች መቆጣጠር ያልቻለው የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት ስምምነት ካልተቀለበሰ በግዛቷ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲቆይ እንደማትፈልግ ባለሥልጣናቷ እየተናገሩ ነው።

ይህ የሶማሊያ መንግሥት ውሳኔ የአፍሪካ ኅብረትን እና ምዕራባውያንን አሳስቧቸዋል። ምክንያቱም በአገሪቱ የተሰማራውን ኃይል በማዳከም አልሻባብ እንዲጠናከር እና ይዞታውን እንዲያሰፋ ዕድል ይፈጥርለታል በሚል ነው።

የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሌሎቹ አገራት ተለይቶ ግዛታቸውን ለቆ እንዲወጣ ቢጠይቁም፤ የአገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ ግዛት እና ጁባላንድ ተቃውመውል። የግዛቶቹ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ ከወጣ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ሊከሰት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ሚና

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመፍጠር እና ወደብ የመጠቀም መብት ለማግኘት እየሞከረች መሆኑ በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት አሻክሮታል።

በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰኢድ (ቦሐሺም) ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ውል ሞቃዲሾን አዲስ አበባ ላይ እምንት እንዳይኖራት አድርጓል ይላሉ።

በዚህም ሳቢያ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ኢትዮጵያን ሉአላዊነቱን ጥሷል ብሎ በማሰቡ እና ስጋት ስለተፈጠረበት ከግዛቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲወጣ ለመጠየቅ ምክንያት እንደሆነው ይናገራሉ።

የሶማሊያ ሠራዊትን ለማጠናከር የተለያዩ ወገኖች ለዓመታት የዘለቀ ድጋፍ ቢደረግም የሶማሊያ ግዛቶች እና ምዕራባውያን ሠራዊቱ በራሱ አልሻባብን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ስለመኖሩ የሶማሊያ ግዛቶች እና ምዕራባውያን እርግጠኞች አይደሉም።

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ግን “ሶማሊያ በቂ አቅም አላት። አልሸባብን ማገድ ትችላለች፣ የአልሸባብ ጉዳይ ለሶማሊያውያን ከተተወ ራሳቸው ሊታገሉት እና ሊያሸንፉት ይችላሉ” የሚል ዕምነት አላቸው።

“የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ ትልቅ ሚና አለው” የሚሉት በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ የፓለቲካ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አገናኝ ከበደ ግን በዚህ ሀሳብ አይሰማሙም።

ለዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ተሰማርቶ የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት ካለው ልምድ እና ብቃት አንጻር የሶማሊያን መንግሥት በመጠበቅ እና በማጠናከር ያለው ሚና የሚተካ አይደለም ሲሉ ይገልጹታል።

“ምንም እንኳን ጉልህ ለውጥ ታየ ባይባለም ሶማሊያ ለደረሰችበት አንጻራዊ መረጋጋት [የኢትዮጵያ ሠራዊት] ሚናው በጣም ከፍተኛ ነው። ሠራዊቱ ከሶማሊያ ቢወጣ ነገሮች ከባድ ነው የሚሆኑት።”

የኢትዮጵያ ሠራዊት መውጣት. . .

በሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ከኢትዮጵያ ወታደሮች በተጨማሪ የቡሩንዲ፣ የጂቡቲ፣ የኬንያ እና የኡጋንዳ ሠራዊት አባላት ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮቿ በኅብረቱ በኩል እና ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ባላት ስምምነት አማካይነት ተሰማርተው ይገኛሉ።

ቢያንስ ሦስት ሺህ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ኅብረት በኩል ለሰላም ማስከበር የተሰማሩ ሲሆን፣ ከአምስት አስከ ሰባት ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በሁለቱ አገራት ስምምነት በሶማሊያ ተሰማርተዋል። ይህም ከፍተኛ ቁጥር ከመሆኑ ባሻገር ሚናውም በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የተሠራጨ ነው።

አልሻባብ ሞቃዲሾን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከባድ ጥቃቶችን ከመፈጸሙ ባሻገር ሰፊ የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጥሮ ይገኛል። ረዳት ፕሮፌሰር አገናኝ እንደሚሉት የሶማሊያ ሠራዊት እና የፀጥታ ኃይል ተጠናክሮ ኃላፊነቱን መወጣት ሳይችል የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአገሪቱ የሚወጣ ከሆነ መዘዙ ከሶማሊያ አልፎ አካባቢውንም የሚነካ ይሆናል።

“አልሸባብ የሽብር ጥቃቱን እንደገና ያስፋፋል፤ ሶማሊያን ሊቆጣጠር ይችላል፤ ከሶማሊያ አልፎም ለምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የደኅንነት እና የሰላም ስጋት ይሆናል” በማለት የኢትዮጵያ ሠራዊት በአሁኑ ወቅት መውጣቱ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጭምር ትልቅ ጉዳት ይኖረዋል ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የደኅንነት ባለሙያዎችን እና ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ እንደዘገበው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያን ለቆ የሚወጣ ከሆነ የአገሪቱ ኃይሎች የሚፈጠረውን ክፍተት የመሙላት አቅም ስለማይኖራቸው ሶማሊያን የበለጠ አለመረጋጋት ውስጥ ሊከታት ይችላል።

በሶማሊያ ከተሰማሩት አገራት ወታደሮች መካከል ቀላል የማይባል ሚና ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያ መንግሥት እንደፈለገው ከግዛቱ ለቆ የሚወጣ ከሆነ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው የአልሻባብ ተዋጊዎች ክፍተቱን ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት እና በምዕራባውያን ድጋፍ እንዲጠናከር ለዓመታት ሲሠራበት የነበረው የሶማሊያ መንግሥትን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊከተው ይችላል።

By BBC News አማረኛ

The BBC is the world’s leading public service broadcaster

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው