ምባፔ ፈረንሳይ ኦስትሪያን 1 ለ 0 ባሸነፈችበት የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ ጉዳት ደርሶበታል ፡፡ የሎስብላንኮዎቹ አሰልጣኝ ዴሻምፕ ምባፔ በቀጣይ ጨዋታዎች የሚኖረውን ተሳትፎ ለመወሰን ጊዜው ገና ነው ብለዋል፡፡ 

የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች ትላንት ቀጥለው ሲካሄዱ ኦስትሪያን የገጠመችው ፈረንሳይ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች፡፡ 

በጨዋታው የቡድኑ አምበል የ25 አመቱ አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በቅጣት ምት የተገኘ ኳስ በጭንቅላቱ ለመግጨት ሲሞክር ከኦስትሪያው ተጫዋች ኬቨን ዳንሶ ትከሻ ጋር ተጋጭቶ አፍንጫው ተሰብሯል፡፡ 

ከግጭቱ በኋላ ፈረንሳይ ምባፔን በኦሊቨር ጂሩድ ለመቀየር ብትፈልግም ቅያሪው ሳይከነወን ጨዋታው ቀጥሏል፡፡

ከጉዳቱ በኋላ ቅያሪው በፍጥነት አለመከናወኑን ተከትሎ ጨዋታውን እየተደረገ ባለበት መሀል ሜዳ ላይ ያለፍቃድ የተቀመጠው ምባፔ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል፡፡ 

አደጋውን ተከትሎ ተጨዋቹ ወደ ዱስልዶርፍ ሆስፒታል ተወስዶ አፍንጫው መሰበሩን ዶክተሮች አረጋግጠዋል፡፡  

አሁን በሚገኝበት ሁኔታ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና እንደማያስፈልገው የገለጹት ዶክተሮች ከተወሰነ የህክምና ክትትል በኋላ ጭምብል (ማስክ) አድርጎ መጫዋት የሚችልበት እድል ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በካምፕ የሚገኘው ምባፔ በቀጣዩ አርብ ፈረንሳይ ከኔዘርላንድስ ጋር ላለባት ወሳኝ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አልተረጋገጠም፡፡ 

 ከጨዋታው በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕ አምበላቸው ክፉኛ መጎዳቱን ገልጸው በቀጣይ በውድድሩ የሚኖረውን ተሳትፎ እስከ አርብ ድረስ የምናገኛቸው የህክምና ክትትል ውጤቶች ይነግሩናል ነው ያሉት፡፡ 

አሰልጣኙ አክለውም “የምባፔ መኖር ለቡድኑ ጥንካሬ ወሳኝ ነው የጉዳት መጠኑ ከከፋ ግን ያለእርሱ እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

 የ25 አመቱ የቀድሞ የፒኤስጂ ኮከብ ኪሊያን ምባቤ ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በተሰለፈባቸው 80 ጨዋታዎች 47 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

በዘንድሮ የዝውውር መስኮት ከፓሪስ ወደ ማድሪድ የተዘዋወረው ተጫዋቹ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በሪያል ማድሪድ ማልያ የምንመለከተው ይሆናል።

By Al Ain Amharic News

አል ዐይን ኒውስ ሁሉን አቀፍ ሽፋን የሚሰጥ እና የዓለም ክስተቶችን በወቅቱና በጊዜው ለተከታዮቹ ያቀርባል፡፡

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው