“ክለቦቻችንን እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ከውድድር ርቀው የነበሩትን የትግራይ ክለቦች መልሶ ለማቋቋም ዛሬ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል ታላቅ የቴሌቶን መርሐግብር ይደረጋል።

በ2013 የመጀመሪያ ወራት በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከውድድር ርቀው የመፍረስ አደጋ የተጋረጠባቸውን ክለቦች መልሶ ለማቋቋም ከአንድ ዓመት በፊት በአትሌት ደራርቱ ቱሉ የክብር አምባሳደርነት ተጀምሮ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበው የትግራይ ክለቦችን በፋይናንስ የማገዝ ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ ክልሎች ፣ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ፣ ባለሃብቶች ፣ የተለያዩ በርካታ ወገኖች ፣ የስፖርት ቤተሰቦች እና የመገናኛ ብዙኀንን የሚያሳትፍ የቴሌቶን መርሐግብር ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል የሚደረግ ይሆናል።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሊጉ የነበሩትን መቀለ ሰባ እንደርታ ፣ ወልዋሎ እና ስሑል ሽረ ወደ ሊጉ እንዲመለሱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባሳወቀው መሠረት ክለቦቹ ለከርሞ የሚሆናቸውን ዝግጅት ለማድረግ በቅድሚያም በፋይናንስ ራሳቸውን ለማጠናከር በማለም “ጋንታታትና ንድሕን/ክለቦቻችንን እንታደግ” ስፖርት ለሁሉም የትግራይ ክለቦች ፣ በእናንተ ውስጥ እኛም አለን ፤ ስፖርት ለሰላም ፣ ስፖርት ለፍቅር ፣ ስፖርት ለሀገር አንድነት በሚል መሪ ቃል ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከናወን ይጠበቃል።

ዝግጁቱን ለሕዝብ ለማድረስም መገናኛ ብዙኀን በቦታው ተገኝተው እንዲዘግቡ አዘጋጆቹ ጥሪ አድርገዋል።

By Soccer Ethiopia ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የኦንላይን ሚድያ ነው።