ዛሬ ለፓርላማ የተመራው፤ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የአዋጅ ማሻሻያ ምን ይዟል? 
ዛሬ ለፓርላማ የተመራው፤ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የአዋጅ ማሻሻያ ምን ይዟል? 

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የባንክ ስራ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራ። የአዋጅ ማሻሻያው፤ የባንክ አገልግሎት ዘርፍን “ለመምራት፣ የፈቃድ አሰጣጥን ለመወሰን እና ለማስተዳደር” የሚያስችል ሆኖ እንደተዘጋጀ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 7፤ 2016 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የባንክ ስራ አዋጅ ማሻሻያን ጨምሮ አምስት የአዋጅ ረቂቆች ለፓርላማ እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳልፏል። የባንክ ስራን መፍቀድ እና መቆጣጠርን የተመለከተ አዋጅ በመጀመሪያ የወጣው በ1986 ዓ.ም ነበር። ይህ አዋጅ በ2000 ዓ.ም በጸደቀ “የባንክ ስራ አዋጅ” ተተክቷል።

አሁን በስራ ላይ ያለው “የባንክ ስራ አዋጅ”፤ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን አካትቶ ከአራት ዓመት በፊት በፓርላማ የጸደቀ ነው። ይህ አዋጅ በድጋሚ እንዲሻሻል የተደረገው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚከፍት ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በነሐሴ 2014 ዓ.ም መወሰኑን ተከትሎ ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ፤ የባንክ ዘርፉን “በጥንቃቄ በተዘጋጀ የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት መክፈት የዘርፉን ተወዳዳሪነት እና ቅልጥፍና” ያሻሽላል ተብሎ እንደሚታመን ያስረዳል። እርምጃው “ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል” የሚል ተስፋን የሰነቀ አገላለጽም በአዋጅ ማሻሻያው መግቢያ ላይ ሰፍሯል።

ማሻሻያው በፓርላማ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል፤ 31 የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ አቻዎቸው ጋር በኢትዮጵያ ገበያ እንዲወዳደሩ ያደርጋል። እስከ ሰኔ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ፤ ከሀገር ውስጥ ባንኮች አጠቃላይ ሀብት 49.5 በመቶ ድርሻ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። የፋይናንስ ዘርፉን የመቆጣጠር ኃላፊነት በተጣለበት ብሔራዊ ባንክ፤ ብቸኛው “ግዙፍ” የተባለ ተቋም ይኸው መንግስታዊ ባንክ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የሪፎርም እና የካፒታል ማሳደጊያ ዕቅድ” ላይ ተወያይቶ ወደ ተግባር እንዲገባ “በሙሉ ድምጽ ወስኗል።” የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ጉዳዮች መካከል፤ “የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚረዳ የመንግስት የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል” የሚለው እንደሚገኝበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።

ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሚያዝያ ወር ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተቀማጭ 48.7 በመቶ፣ በካፒታል ደግሞ 27.5 በመቶ ድርሻ አለው። በብሔራዊ ባንክ መካከለኛ በሚል የተደለደሉ አምስት ባንኮች፤ በጠቅላላ ሀብት ረገድ 28 በመቶ፣ በተቀማጭ 29.4 በመቶ፣ በካፒታል ደግሞ 31.0 በመቶ ድርሻ ያላቸው ናቸው።

አዋሽ፣ ዳሸን፣ አቢሲኒያ፣ ሕብረት እና ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፤ “መካከለኛ” የሚለውን ደረጃ ያገኙ አምስት ባንኮች ናቸው። “ትናንሽ” የተባሉ 24 ባንኮች አጠቃላይ ሀብት፤ ከኢንዱስትሪው 22.5 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን የሰበሰቡት ተቀማጭ 21.9 በመቶ ነው።

አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ማሻሻያ፤ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ መሆኑ “የእነዚህን ትናንሽ ባንኮች ህልውና ይፈታተናል” የሚል ስጋት ከዘርፉ ባለሙያዎች ይደመጣል። በአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ መሰረት፤ የውጭ ባንኮች “በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት” ተቀጥላ ባንክ ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ወይም የውክልና ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ይፈቀድላቸዋል።

የአዋጅ ማሻሻያው፤ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የድርሻ ባለቤት እንዲሆኑ ጭምር ይፈቅዳል። የውጭ ሀገር ዜጎች እና የውጭ ንብረት የሆኑ የኢትዮጵያ ድርጅቶች፤ በአንድ ባንክ የሚኖራቸው የአክሲዮኖች ድርሻ 40 በመቶ ብቻ ሆኖ በአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ ተገድቧል።

የውጭ ሀገር ዜጎች እና የውጭ ንብረት የሆኑ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች፤ በባንክ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት በውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ (FDI) በውጭ ምንዛሬ ብቻ እንደሚሆን በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተቀምጧል። የባንክ ሥራ አዋጅ ማሻሻያው ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል የኬንያው ኬሲቢ እና ስታንዳርድ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሊገቡ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የውጭ ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲገዙ፤ ብሔራዊ ባንክ “በልዩ ሁኔታ” ሊፈቅድ እንደሚችል በአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ይህ የሚደረገው ግን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ “ስትራቴጂክ ጥቅም” ካለው ወይም ችግር ውስጥ ለገባ ባንክ መፍትሔ ለማበጀት እና የፋይናንስ ስርዓቱን መረጋጋት ለመጠበቅ እንደሆነ የአዋጅ ማሻሻያው ይደነግጋል።

የውጭ ባንክ ተቀጥላ ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ፤ ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን ንብረት በባለቤትነት መያዝ እንደሚችሉ የሚፈቅድ ድንጋጌም ለፓርላማ በተመራው የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ተካትቷል። የውጭዎቹ ባንኮች የወረሷቸው እና በዋስትና የያዟቸው ንብረቶች ጉዳይ፤ አግባብነት ባለው የኢትዮጵያ ህግ መሰረት የሚወሰን እንደሚሆን ይኸው የአዋጅ ረቂቅ ያትታል።

በአዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ፤ ባንኮች በዋና ስራ አስፈጻሚ እና ከፍተኛ የስራ አስፈጻሚ ኃላፊነቶች የውጭ ዜጎችን የመቅጠር ዕድል ተሰጥቷቸዋል።

ከአንድ ባንክ ሰራተኞች ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚኖራቸው ምጣኔ፤ ወደፊት በሚወጣ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ የሚወሰን መሆኑም ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

By Ethiopia Insider

Ethiopia Insider is your news, analysis, features and entertainment website.