የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚደረገው መጠነ ሰፊ ጥቃት ሊቆም እንደሚችል ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው በሰሜኑ በኩል ሄዝቦላ ለደቀነው የደህንነት ስጋት ምላሽ ለመስጠት በጋዛ የሚገኘውን ጦሯን ልትቀንስ እንደምትችል አስታውቀዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ኔታንያሁ፤ ቻናል 14 ከተባለ የእስራኤል ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የጥቃቱን መጠን እንቀንሳለን ማለት ጦርነቱ አብቅቷል ማለት አይደለም ብለዋል።

በጋዛ ሀማስን ሙሉ ለሙሉ እስከምናስወግድ እና ታጋቾችን እስከምናስመልስ ውጊያው ይቀጥላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሰሜን ድንበር ላለው ስጋት መዘጋጀት በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሃማስ ጋር ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከፊል ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ በጦርነቱ መቀጠል ላይ ግን አሁንም አቋማቸውን አለመቀየራቸውን ነው አስረግጠው የተናገሩት።

እየሩሳሌ እና ቴል አቪቭን ጨምሮ በስምንት የእስራኤል ከተሞች ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ እና ሕዝባዊ ተቃውሞ እያስተናገዱ የሚገኙት ኔታንያሁ፤ ይህኛው ውሳኔያቸውም ነቀፌታን አስከትሎባቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው ሀማስ፤ ኔታንያሁ ለንግግር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እንዲሁም አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነትም ሆነ የጸጥታው ምክር ቤት ያጸደቀውን የውሳኔ ሃሳብ እንደማይቀበሉ ግልጽ ምላሽ የሰጡበት እንደሆነ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የታጋች ቤተሰቦች ማህበር በበኩሉ የኔታንያሁ አስተዳደር ታጋቾችን ከሀማስ እጅ ሳያስለቅቅ ከጋዛ ጦሩን የሚያስወጣ ከሆነ ትልቅ ሀገራዊ እና ወታደራዊ ውድቀት ማሳያ ነው ብሏል።

የጥቅምት ሰባቱን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ስታሰማራ ታጋቾችን ማስመለስ፣ ሀማስን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እና ድጋሚ ከፍልስጤም ጥቃት እንደማይሰነዘር ማረጋገጥ የሚሉ አላማዎችን ይዞ እንደነበር ይታወሳል።

የታጋች ቤተሰቦች ማህበር ባወጣው መግለጫ ታድያ “የስምንት ወራቱ ጦርነት ውጤት ምን እንደሆነ አስተዳደሩ ሊገልጽ ይገባል፤ ሀማስ አሁንም አልጠፋም ታጋቾችም ለስምንት ወራት በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፤ ስለዚህ ዘመቻው ያመጣውን ስኬት አስተዳደሩ እንዲመልስልን እንፈልጋለን” ነው ያለው።

14 ሺህ የሀማስ ታጣቂዎችን መግደሉን ያስታወቀው የእስራኤል ጦር በበኩሉ፤ ሀማስን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም ሲል መናገሩ ይታወሳል።

የጦሩ ቃል አቀባይ ሀማስ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ያለ “አይዲዎሎጂ” ነው ሀማስን ማጥፋት ማለት ሙሉ የጋዛ ነዋሪዎችን ማጥፋት እንደማለት ነው በሚል ተናግረዋል። አክለውም “ከፍልስጤም ሊኖር የሚችል የጥቃት ስጋትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት አይቻለም፤ የጥቅምት ሰባቱ አይነት ጥቃት እንዳይከሰት ማድረግ የምንችለው የተጠናከረ ዝግጅት እና ጥበቃ በማድረግ ብቻ ነው” ብለዋል።

በመከላከያ ጦሩ እና በኔታንያሁ አስተዳደር መካከል ያለው ጥቃት እየሰፋ ባለበት ቃል አቀባዩ አደረጉት የተባለው ንግግር በአስተዳደሩ ዘንድ ቁጣን አስነስቷል። የኔታንያሁ መንግሥት ለዚህ በሰጠው ምላሽም የሀማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስኪበታተን ድረስ ውጊያው ይቀጥላል ብሏል።

ወደ ሰሜን ትኩረቴን አዞራለሁ ያለው የኔታንያሁ አስተዳደር፤ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው መመለስ እና የድንበር ጥበቃውን ማጠናከር አላማው እንደሆነ ግልጽ አድርጓል ሲል የዘገበው አልዓይን ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

By Ethiopia Press Agency

Ethiopian Press Agency is a public media enterprise operating in Ethiopia.