ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ፊሽካ በጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች በሜዳዉ ላይ ያለዉን እንቅስቃሴ በበላይነት ለመቆጣጠር የየራሳቸዉን ጥረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ፤ ተመጣጣኝ በነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ከግማሽ ሰዓታት በኋላ ግብ ተቆጥሮበታል።

በዚህም በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ በቀኝ መስመር በኩል ለአማኑኤል ከሰነጠቀለት በኋላ ተጫዋቹ ወደ ሳጥን ያሻማዉን ኳስ ነጥሮ ያገኘዉ አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን ኢትዮጵያ ቡና መሪ ማድረግ ችሏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን መድኖች በወገኔ ገዛኸኝ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት ከጫፍ ደርሰዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ አስገራሚ ብቃት ሙከራቸዉ ከሽፎባቸዋል።

ከዕረፍት መልስ ያሬድ ዳርዛን ቀይረዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት መድኖች ቅያሬያቸዉ ሰርቶ ወዲያው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የቡና ተከላካዮች በሰሩት ስህተት የተገኘዉን ኳስ ተቀይሮ የገባዉ ያሬድ በግሩም ብቃት ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ከቀኝ በኩል አማካዩ አብዱልከሪም ወርቁ የመድንን ተጫዋቾች አታሎ አልፎ ሳጥን ዉስጥ በቀጥታ ወደ ግብ የመታትን ኳስ የግቡ አግዳሚ ቢመልሳትም ነገር ግን ኳሷን የመድኑ ተከላካይ አብዱልከሪም መሐመድ በራሱ መረብ ላይ አሳርፏታል።

በ76ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ አቡበከር ሳኒ ከዮናስ ገረመዉ በተቀበለዉ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ በረከት እንደምንም ኳሷን ይዞበታል። ከዚህ ሙከራ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ አቡበከር ኑራ ኳሷን አዉጥቶባቸዉ በመርሐግብሩም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከትበት ጨዋታዉ በቡናማዎቹ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በርካታ ጎሎች በተቆጠሩበት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የዋንጫ ተፎካካሪዉ መቻል ሲዳማ ቡናን አራት ለአንድ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ አመሻሽ አስራ ሁለት ሰዓት ሲል በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሀያ እና ሰላሳ ደቂቃዎች ያን ያህል ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎችን መመልከት ባንችልም ነገር ግን በእንቅስቃሴ ረገድ ሁለቱም ክለቦች ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።

የግሩም ሀጎስን እና ማይክል ኪፕሮፕን ሙከራዎች ብቻ ባስመለከተን የጨዋታዉ የመጀመሪያ አጋማሽ በ41ኛዉ ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ አማካዩ ሽመልስ በቀለ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ምንይሉ ወንድሙ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መቻል በአጋማሹ መገባደጃ ላይ መሪ ማድረግ ችሏል። ከዕረፍት መልስ መቻሎች ዳግም በፍጥነት መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም ሽመልስ በቀለ ከማዕዘን ያሻማዉን ኳስ በሀይሉ ግርማ ወደ ግብነት ቀይሮ የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።

የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር በመቻሎች ብልጫ እየተወሰደባቸዉ የቀጠሉት ሲዳማዎች የተጫዋቾች ለዉጥ ካደረጉ በኋላ በ65ተኛዉ ደቂቃ ላይ በብርሀኑ በቀለ አማካኝነት ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ግብ አስቆጥረዉ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ሞክረዋል። ነገር ግን በዕለቱ ድንቅ የነበሩት መቻሎች በ73ተኛዉ ደቂቃ ላይ በጨዋታዉ ድንቅ በነበረዉ ከነዓን ማርክነህ ሶስተኛ ግብ አስቆጥረዉ የሲዳማ ማንሰራራት ላይ ዉሀ ቸልሰዉበታል።

በመጨረሻም ሁለቱም ክለቦች ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን በመሄድ ዕድሎችን ለመፍጠር መጣር የቀጠሉ ሲሆን ፤ በዚህም መቻሎች ጥረታቸዉ ፍሬ አፍርቶ በከነዓን አማካኝነት አራተኛ ግብ አስቆጥረዉ ጨዋታዉን አራት ለአንድ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።