አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ቻይና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እንደሚሠሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያና የቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት ትውውቅ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ (ዶ/ር) መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ቻይና ለረጅም ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነት አላቸው።

ይህ መድረክም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ግንኑነት ለማጠናከርና ያሉ ንግድና ኢንቨስትመንት እድሎችን አሟጦ ለመጠቀም ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መስኮች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከርና በትብበብር ለመሥራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ አሁንም በርካታ የቻይና ኢንተርፕራይዞች በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍላጎት እያሳዩ ነው።

ይህም ግብርና፣ ህክምና፣ ኮንስትራክሽንና የግንባታ እቃዎች እንዲሁም ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎችን የሚያጠቃልል ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋነኛ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን የሚያስችል አቅም እንዳላት እናምናለን ያሉት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፤ ቻይናውያን ባለሀብቶችም ሀገራችን ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አካል እንድትሆኑ እጋብዛለሁ ብለዋል።

በሀገሪቱ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ የቤጂንግ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ በቀጣናው ያለውን ትልቅ የገበያ እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥትም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጨምረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ያንግ ይሀንግ በበኩላቸው፤ ቻይና ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ብለዋል።

ቻይና በኢትዮጵያ ዋንኛዋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት የፓይና ኢንተርፕራይዞች በ200 ሚሊዮን ዶላር አንድ መቶ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት አድርገዋል፤ በዚህም ለ19 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በቀጣይነትም በመሠረተ ልማት፣ ባዮ ቴክኖሎጂና በሌሎችም መስኮች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸው፤ መድረኩ ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ኤምባሲውም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲጠናከርና ተጠቃሚነታቸው ከፍ እንዲል ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው፤ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ የምትገኝና የአህጉሩ መግቢያ በር መሆኗን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን አብራርተዋል። በዚህም የመሬትና የፋይናንስ፣ መሠረተ ልማት እና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ አድርጓል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ስትራቴጂክ ቦታና በሌሎችም ምቹ ሁኔታዎች ለቢዝነስና ኢንቨስትመንት ትልቅ መዳረሻ አድርጓታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሳተፉ ካሉ የውጭ ኢንቨስተሮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ሀገሪቱ ያላት አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ ስላልዋለ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የተካሄደው ምክክርና የተፈረመው ስምምነት ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተው፤ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል።

ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ፕሮሞሽን ምክር ቤት ቤጂንግ ቅርንጫፍ ጋር፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከቤጂንግ ዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ጋር ያደረጉትን ጨምሮ ሌሎችም የኢትዮጵያና የቻይና ተቋማትና ማህበራት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

By Ethiopia Press Agency

Ethiopian Press Agency is a public media enterprise operating in Ethiopia.