የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታሪካዊ ነው በተባለለት የፍርድ ሂደት በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ መባላቸውን ተከትሎ እጅግ የናጠጡ የሪፐብሊካን ፓርቲ ለጋሾች ከኋላቸው መሰለፋቸው እየተነገረ ነው።

በመጪው ዓመት ኅዳር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ይሆናሉ የሚባሉት ትራምፕ፤ ለቀድሞ የወሲብ ፊልም ተዋናይት ስቶርሚ ዳንኤልስ አፍ ማዘጊያ የተከፈለውን ገንዘብ ለመደበቅ መዝገቦችን በማጭበርበር ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ከጆ ባይደን እና ከዲሞክራቶች የገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ አንጻር ወደኋላ የቀሩት ትራምፕ፤ የፍርድ ውሳኔው በምርጫ ቅስቀሳ ዙሪያ አዲስ ጉልበት እንደፈጠረላቸው ታውቋል። ከውሳኔው በኋላ ባሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ወደ 53 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻላቸው ተነግሯል።

እስራኤላዊቷ አሜሪካዊት የካሲኖ ቢሊየነር ሚርያም አደልሰን በዚህ ሳምንት የትራምፕን የምርጫ ዘመቻ በብዙ ሚሊዮን ዶላር እንደምትደግፍ ታሳውቃለች ተብሎ ይጠበቃል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ አዴልሰን ፕረዘርቭ አሜሪካን ለሚባለው የፖለቲካ ኮሚቴ ገንዘቡን ትለገሳለች። ኮሚቴው የተመረጡ ዕጩዎችን ለመደገፍ ያልተገደበ ገንዘብ ማውጣት ይችላል ተብሏል።

ምን ያህል ገንዘብ ለማውጣት እንዳቀደች ባይታወቅም፣ ፖሊቲኮ እና ሌሎች የአሜሪካ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት ከሆነ ግን ከ2020 ምርጫ በፊት በአደልሰን እና በሟች ባለቤቷ ሼልደን ለፕሪዘርቭ አሜሪካ ከሰጡት ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሌሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። ባለፈው ሳምንት የጥፋተኝነት ውሳኔው መተላለፉን ተከትሎ በርካታ ቢሊየነሮች ለትራምፕ የድጋፍ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ከእነዚህም መካከል የሲሊከን ቫሊ ባለሀብቱ ዴቪድ ሳክስ በኤክስ ላይ “በዚህ ምርጫ አንድ ጉዳይ ብቻ ነው ያለው፤ ይህም የአሜሪካ ሕዝብ አሜሪካ የተዳከመች ትንሽ አገር ትሆናለች ወይ የሚለው ጉዳይ ነው” ሲል አስፍሯል።

ሳክስ እና ሌላኛው ባለሀብት ቻማት ፓሊሃፒቲያ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ለትራምፕ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ እንደሚያዘጋጁ ተነግሯል። ተሳታፊዎች እስከ 300 ሺህ ዶላር እንዲያዋጡ እየተጠየቁ ነው ተብሏል።

የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ተብለሎ የሚጠበቀው ሌላኛው ለጋሽ እና የሄጅ ፈንድ ሥራ አስኪያጅ ቢል አክማን፤ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ስለመደገፍ በሚቀጥሉት ቀናት በኤክስ ላይ ውሳኔውን እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

በካፒቶል ሂል የተፈጠረውን ግርግር ተከትሎ ትራምፕ “ሁሉምንም አሜሪካውያን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው” ሲል ከሦስት ዓመታት በፊት ቢናገርም፣ የፋይናንስ ባለሙያው ንግግሩን በማለዘብ ለቀድሞው ፕሬዝዳንት በበይነ መረብ የድጋፍ ቃላትን አዥጎድጉዷል።

የብላክስቶን ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና በዎል ስትሪት ካሉ ታዋቂ ቢሊየነሮች አንዱ የሆነው ስቲቭ ሽዋርዝማን በምርጫው ትራምፕን እንደሚደግፍ ከወዲሁ አስታውቋል።

ልክ እንደ አክማን ሁሉ ሽዋርዝማንም ከዚህ ቀደም ራሱን ከቀድሞው ፕሬዝዳንት አግልሎ ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ግን “የእኛ የኢኮኖሚ፣ የስደተኞች እና የውጭ ፖሊሲ አገሪቷን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየወሰዷት ነው የሚለውን የአብዛኞቹ አሜሪካውያን ስጋት” እንደሚጋራ ሽዋርዝማን ተናግሯል።

በተጨማሪም “በአስደናቂ ፍጥነት እየጨመረ የሚገኘው ፀረ-ሴማዊነት በመጪው ምርጫ ላይ በሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች ላይ ትኩረት እንዳደርግ አሰገድዶኛል” ብሏል።

እስካሁን ድጋፋቸውን ለትራምፕ ከሰጡ ታዋቂ ቢሊየነሮች መካከል የሄጅ ፈንድ መሥራቾቹ ጆን ፖልሰን እና ሮበርት ሜርሰር ይገኙበታል። ሃሮልድ ሃም እና በካሲኖ ባለሃብትነቱ ስመ ገናና የሆነው ስቲቭ ዊን ይገኙበታል።

ቢሊየነሩ ኔልሰን ፔልዝ ከካፒቶል ሂል የትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙት ጥቃት በኋላ በ2020 ትራምፕን በመምረጡ መጸጸቱን ቢገልጽም፣ አሁን ሃሳቡን ለውጦ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በመጋቢት ወር በፍሎሪዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ጋብዟቸዋል።

ከዚህ ቀደም ለሁለቱም ዕጩዎች ምንም እንደማይለግስ የተናገረው ኤሎን መስክ፣ ከትራምፕ ጋር የቀጥታ ሥርጭት ለማዘጋጀት ዕቅድ አውጥቷል።

በተመሳሳይ ቢሊየነሩ የሪፐብሊካን ፓርቲ ለጋሽ ፒተር ቲኤል ለትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ገንዘብ እንዲለግስ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን እና በዚህ ምርጫ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ እንደማያደርግ ተነግሯል።

ሻውን ማጓየር በበኩሉ ትራምፕ ላይ ባለፈው ሳምንት የተሰጠውን የጥፋተኝነት ብይን ተከትሎ ሂደቱ ፍትሐዊ አልነበረም በሚል በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ 300 ሺህ ዶላር መለገሱን አስታውቋል።

ማጓየር በኤክስ ላይ በለጠፈው ረዥም ጽሑፍ፤ በባይደን አስተዳደር ወቅት አሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣቷ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን “ደካማ” ተሳትፎ ጨምሮ በሌሎችም ምክንያቶች ትራምፕን ለመደገፍ መወሰኑን ዘርዝሯል።

“ፕሬዝዳንት ትራምፕ በከባድ ወንጀል ተከሰው የእስር ቅጣት ሊፈረድባቸው የሚችልበት ዕድል አለ። በግልጽ ለመናገር እኔ እሱን የምደግፈው አንድም በዚህ ምክንያት ነው። የፍትሕ ሥርዓታችን እሱን ለማጥቃት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብዬ አምናለሁ” ብሏል።

ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የባይደን ቡድን ማሰባሰብ የቻለው ገንዘብ ከትራምፕ ይበልጣል።

በሚያዝያ ወር መጨረሻ 192 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገባ፣ የትራምፕ ግን 93.1 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

በተመሳሳይ ወር ትራምፕ ያገኙት ድጋፍ 76 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በዚህ የምርጫ ገቢ ማሰባሰቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራቶችን የበለጡበት ወር ሆኗል። ባይደን 51 ሚሊዮን ዶላር የሰበሰቡ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በፊት ከተሰበሰበው 90 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ ነው።

በኦሃዮ የሚገኘው የኬዝ ዌስተርን ሪዘርቭ ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ዘመቻ የፋይናንስ ኤክስፐርት የሆኑት ፕሮፌሰር ጀስቲን ቡችለር ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ገንዘብ ውጤቱን አይወሰንም” ብለዋል።

“በምርጫ ዘመቻ ውስጥ የገንዘብ ዋናው ሚና ዕውቅናን ማሳደግ ነው። ሁሉም ሰው ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ማን እንደሆኑ ያውቃል።”

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ከሆነው ሲቢኤስ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ የትራምፕ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ በተለያዩ የሕግ ቁልፍ ሂደቶች ወቅት የመጨመር አዝማሚያ እንዳለው አረጋግጧል።

የጥፋተኝነት ውሳኔው ከመሰጠቱ በፊት ትራምፕ ከፍተኛ ገቢ ያገኙት በኒው ዮርክ ከተማ ክስ በቀረበባቸው በነሐሴ ወር በጆርጂያ እስር ቤት ውስጥ በፖሊስ የተነሱት ፎቶግራፍ በተለቀቀበት ወቅት ነው።

ቢቢሲ በገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻው ላይ አስተያየት ለማግኘት የትራምፕ እና የባይደን የምርጫ አካላት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል

By BBC News አማረኛ

The BBC is the world’s leading public service broadcaster

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው