ባህርዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ አዳማ ከተማን ሲያሸንፍ ፤ ሀድያ ሆሳዕናም ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል !!
ባህርዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ አዳማ ከተማን ሲያሸንፍ ፤ ሀድያ ሆሳዕናም ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል !!

በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ገና በጊዜ ማለትም በ3ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል። በዚህም አቤነዜር ሲሳይ ከግራ መስመር በኩል ወደ ዉስጥ ያቀበለዉን ኳስ ያገኘዉ ኤልያስ ለገሰ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አዳማ ከተማ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የጣና ሞገዶቹ ወደ ጨዋታዉ የመለሳቸዉን ግብ አግኝተዋል። በዚህም የፊት መስመር ተጫዋቹ ቸርነት ጉግሳ እየገፋ ሄዶ ለአማካዩ ያብስራ ያቀበለዉን ኳስ ተጫዋቹ ከርቀት ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። ገና በጊዜ ማለትም በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ክለቦች ግብ ማስቆጠር ከቻሉ በኋላ ያን ያህል ሙከራ ባላስመለከተዉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በቶሎ አድናን ረሻድን እና ዮሴፍን ታረቀኝን ቀይረዉ በማስገባት የማጥቃት ሀይላቸዉን ለማጠናከር የሞከሩት አዳማ ከተማዎች በ64ተኛዉ ደቂቃ ላይ ዳግም መሪ መሆን ችለዋል። በዚህም የባህርዳሩ ግብ ጠባቂ የሰራዉን ስህተት ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ ኤልያስ ለገሰ ለዮሴፍ ታረቀኝ አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን በግሩም ብቃት ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል።

በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ ተጭነዉ መጫወት የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች በ85ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአብስራ ተስፉየ ክሮስ ያደረገለትን ኳስ ወንደሰን ጥላሁን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን ባህርዳር ወደ አቻነት መመለስ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ዳግም ጫና ፈጥረዉ መጫወት የቀጠሉት ባህርዳሮች በ90+1 ላይ አሸናፊ መሆን የቻሉበትን ሶስተኛ ግብ ማግኘት ችለዋል። በዚህም አምሳሉ ሳሌ ያቀበለዉን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብ ሲመታ ኳሷን ፍቅሩ አለማየሁ ወደራሱ መረብ ላይ አሳርፎ ባህርዳሮች አሸናፊ እንዲሆኑ አስችሏል።

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን ማሸነፍ ችሏል።

በዚህ በሁለቱ ክለቦች የአመሻሽ 12 ሰዓት ጨዋታ ገና በጅምሩ ሀድያ ሆሳዕናዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከግራ መስመር በኩል የተሰጠዉን የቅጣት ምት ኳስ ቴዎድሮስ ታፈሰ አሻምቶ አምበሉ ግርማ በቀለ በጭንቅላት ወደ ግብነት ቀይሮ ገና በጊዜ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ተሻሽለዉ መንቀሳቀስ የቀጠሉት ሀድያዎች በ12ተኛዉ ደቂቃ ላይ አስደናቂ የግብ ዕድል በቴዎድሮስ ታፈሰ አማካኝነት መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የድሬዳዋዉ ተከላካይ ልላኛዉ ተዎድሮስ ሀሙ እንደምንም ብሎ ኳሷን  አዉጥቶባቸዋል። ከዚህ በዘለለ እምብዛም ሙከራዎችን ያላስመለከተን የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ አጋማሽ በዚሁ ፍፃሜዉን አግኝቷል።

ከዕረፍት መልስ በተሻለ ተነሳሽነት ጨዋታቸዉን የጀመሩት ድሬዳዋዎች በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ አጥቂዉ ካርሎስ ዳምጠዉ አማካኝነት ድንቅ የግብ ሙከራ ከቅጣት ምት አድርገዉ የግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ እንደምንም ሲያወጣባቸዉ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ግን ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በዚህም ከቅጣት ምት የተሻማዉን ኳስ ተሸራርፎ ያገኘዉ ቃልዓብ ዉብሸት ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።

በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም በ89ነኛዉ ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍተይ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ሶስተኛ ግብ ሲያስቆጥር ፤ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት ደግሞ አድናን መኪ ለድሬዳዋ ከተማ ማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታዉ በሀድያ ሶስት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።