የኢትዮጲያ የአጥንት ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ በአጥንት ህክምና ሰብ ሰፔሻላይዝድ ያደረጉ የህክምና ባለሙያዎች ከአስር እንደማይበልጡ አስታውቋል።

ከነዚህም መካከል በአጥንት ካንሰር ላይ ሰብ ስፔሻላይዝድ ያደረገ ባለሙያ በኢትዮጵያ ወስጥ አንድ ባለሙያ ብቻ ነው ተብሏል ።

የኢትዮጲያ አጥንት ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በሀገራችን የአጥንት ሀኪሞች ቁጥር አናሳ በመሆኑ ብዙ ታካሚዎች በህክምና ተቋም አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው አካባቢያቸው ባሉ የባህል ህክምና እንደሚጠቀሙ ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩንም ለመቅረፍ ወደ 10 የሚጠጉ ዩኒቨርስቲዎች የአጥንት ህክምናን እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ዮኒቨርስቲዎች በትክክል መምህራንን በሚያበረታቱበት መንገድ አለመቀረፃቸው የአስተማሪዎች እጥረት እንዲያጋጥም መንስኤ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ሆስፒታሎች አካባቢ ደግሞ ኦፕሬሽን ክፍል የሚያስፈልጉ የህክምና ግብአቶች አለመሟላት ለማህበሩ ችግር ሆኖበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ ችግርም ብዙ ታካሚዎች እንደመጡ እንዳይታከሙ እያደረጋቸው እንደሆነ አንስተዋል ፡፡

ማህበሩ ለህክምናው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ከውጪ እርዳታ በመጠየቅ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም እርዳታ በመጠየቅ ግን ሀገር አይቀየርም ብለዋል፡፡

እቃዎቹን ከመግዛትም ባለፈ ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም  ነገሮች ግን በፈለግነው መልኩ ሊሄድልን አልቻለም ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ከመንግስት የሚደረጉ የተወሰኑ ድጋፎች ሚኖሩም በቂ  አለመሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የአጥንት ህክምና ብዙዎችን የአካል ጉዳተኛ እንዳይሆኑ እና ተመልሰው ወደ ነበሩበት የስራ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የሚያደርግ ቢሆንም ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ግን ብዙዎች አካል ጉዳተኛ ሆነው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል ብለዋል ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም አዳጋው እንዳይከሰት ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው ብለን እናምናለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሆስፒታሎችን ማብዛት እና ለሆስፒታሎች አስፈላጊ እቃዎችን ተደራሽ ማድረግ የመንግስትን ትኩረት የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከተመሰረት 30 አመታትን ያስቆጠረው ይህ ማህበር ወደ 3 መቶ የሚጠጉ የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች  እና 2 መቶ50 የህክምና ባለሙያዎችን የያዘ ነው ፡፡

ሐመረ ፍሬው

ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

By Ethio FM 107.8

Ethio FM is news website and popular radio station in Ethiopia.