አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ህጋዊ ውል ምዝገባ ዛሬ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀመር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በሀገሪቱ ያለውን የቤት ኪራይ ችግር ለመፍታት እንዲሁም ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማህበረሰቡ ኑሮና በአጠቃላይ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ከግምት በማስገባት ተዘጋጅቶ መጽደቁ ይታወሳል፡፡

በአዋጁ አስፈላጊነትና አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደረገው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፤ አዋጁን በመመሪያ በማስደገፍ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅቶቹን በማጠናቀቁ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስታውቋል።

በዚህም ከሰኔ 1 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የግል ቤት አከራዮች ከተከራዮቻቸው ጋር ህጋዊ ሰነዶቻቸውን ይዘው በመቅረብ ምዝገባ ማድረግ እንደሚችሉ አስገንዝቧል።

ለምዝገባው የሚያስፈልገውን የሰው ሃይልና መሰረተ ልማት በማደራጀት በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ያደረገው ቢሮው፤ ቤት አከራዮች ህጋዊ የምዝገባ ውል ለመፈጸም ወደ ወረዳ ጽህፈት ቤቶች በሚሄዱበት ወቅት ቤቱ የራሳቸው ስለመሆኑ ወይንም ህጋዊ ተወካይ መሆናቸውን የሚገልጽ ሰነድ ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው ጠቁሟል።

ተከራዮች በበኩላቸው÷ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ወይንም ሌላ ህጋዊ ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ይዘው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

በስራ ሰዓት መመዘግብ የማይችሉ አከራይና ተከራዮች ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በስራ ቀን ማታ ከ12 ሰዓት በኋላ ህጋዊ የውል ምዝገባውን መፈጸም እንደሚችሉም ተገልጿል።

በምዝገባውና አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ቅሬታዎችን በመቀበል ማስተናገድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱም ተነግሯል።

By Fana Broadcasting Corporate S.C

Fana Broadcasting Corporate S.C. (FBC) is a state-owned mass media company operating in Ethiopia.

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው