አዲስ አበባ፡- በቤት ውስጥ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ባለቤት ሊሆኑ አይችልም ሲል የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች የቤት ውስጥ ጥቃት በፈጸሙባቸው ግለሰቦች አካባቢ ድርሽ እንዳይሉም በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ የተጣለባቸው ናቸው።

ውሳኔው በቤት ውስጥ ጥቃት ተጠርጥረው የእግድ ትዕዛዝ በፍርድ ቤት የተጣለባቸው ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ለ30 ዓመት ያህል ሊኖራቸው እንደማይችል አስቀምጧል።

ታችኛው ፍርድ ቤት ይህንን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ “ከሃገሪቱ ታሪካዊ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ባሕል ጋር የማይጣጣም” በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ዓርብ ዕለት ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የጦር መሣሪያዎችን በተመለከተ ባልተለመደ መልኩ እገዳ ማስተላለፉ እንደ ድል ታይቷል።

ዋና ዳኛ ጆን ሮበርትስ ከአንዱ ዳኛ በስተቀር ሁሉም በስምምነት ያሳለፉትን ውሳኔ አሰምተዋል።

የቤት ውስጥ ጥቃት አድራሾችን ትጥቅ የማስፈታት ፖሊሲ “ጤነኛ አዕምሮ ሊያደርገው የሚገባ ነው” ሲሉም ጽፈዋል።

ውሳኔውን በብቸኝነት የተቃወሙት ዳኛ ክላረንስ ቶማስ በወግ አጥባቂነታቸው ይታወቃሉ።

የዛሬው ውሳኔ “‘ሰከንድ አሜንድመንት’ የተሰኘውን ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን የነፃነት መብት አደጋ ላይ የጣለ ነው” ብለዋል።

ዓርብ ዕለት በተላለፈው ውሳኔ መሐልም በሴት ጓደኛው ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በሕዝብ ቦታዎች ላይ ተኩስ በመክፈት የተፈረደበት ዛኪ ራሂሚ የተባለው የቴክሳስ ነዋሪ ጉዳይ ተነስቷል።

ግለሰቡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሴት ጓደኛውን መኪና ውስጥ ጎትቶ በማስገባት ጭንቅላቷን ከመኪናው ጋር እንዳጋጫትና እንዲሁም ጥቃቱን በታዘበ ግለሰብም ላይ ተኩስ ከፍቶ ነበር።

የሴት ጓደኛው በፍርድ ቤት ውሳኔ የእግድ ትዕዛዝ እንዲጣልበትም ማድረግ ችላ ነበር። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የጦር መሣሪያ ፍቃዱ እንዲታገድ እና ምንም አይነት መሣሪያ እንዳይዝ በግለሰቡ ላይ እግድ ቢጥልበትም ይህንን ተላልፎ በሕዝባዊ ቦታ በአምስት ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈቱ ተሰምቷል።

ግለሰቡ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመጣስ ጥፋተኝነቱን ያመነ ሲሆን የስድስት ዓመት እስርም ተፈርዶበታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

By Ethiopia Press Agency

Ethiopian Press Agency is a public media enterprise operating in Ethiopia.