የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት ከነጠቀው ከኢትዮጵያው የ77 ረሀብ ቀጥሎ የሱዳኑ ሊከፋ ይችላል ነው የተባለው። የተዘነጋው ጦርነት በተባለው የሱዳን ግጭት እስከ 2.5 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በረሀብ ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።

በአለም ከ40 አመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ረሀብ በሱዳን ሊከሰት ይችላል ተባለ።

በሱዳን በሁለቱ ጄነራሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ሊያስከፍል እንደሚችል የአለም አቀፍ ተራድኦ ደርጅቶች በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ የተዘነጋው ጦርነት እየተባለ በሚጠራው ግጭት የተከሰተው ረሀብ ከ40 አመታት ወዲሁ በአስከፊነቱ የመጀመርያው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡ 

በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን የሚመራው የሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች ሰብአዊ እርዳታዎች እንዲጓጓዙ ምቹ ሁኔታዎችን ባለመፍጠራቸው ግዙፍ ሰብአዊ ኪሳራ ሊደርስ ይችላል ነው የተባለው፡፡

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ ዋና ሃላፊ ሳማንታ ፓወር የእርዳታ ተሽከርካሪዎችን ጉዞ በማስተጓጎል ሁለቱንም ሀይሎች ከሰዋል፡፡ ሃላፊዋ የሚገባውን ያክል ትኩረት ከአለም አቀፍ መንግስታት እና መገናኛ ብዙሀን የተነፈገው የሱዳን ጦርነት ሰው ሰራሽ ረሀብ እያንሰራራበት እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን መሰረታዊ የሰበአዊ ድጋፎችን ለማድረስ ከሚያስፈልገው ገንዘብ 16 በመቶውን ብቻ እንዳገኝ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ 

የጸጥታው ምክር ቤት በበኩሉ ባሳለፍነው ሳምንት ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በኤልፋሺር ያደረገውን ከበባ እንዲያቆም እና ለሰብአዊ ድጋፍ መተላለፍያዎቸን እንዲከፍት በብሪታንያ የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ሰጥቷል፡፡

 አሜሪካ 315 ሚሊየን ዶላር ለሱዳን ሰብአዊ ድጋፍ ይውል ዘንድ መመደቧን ያስታወቁት የዩኤስኤድ ዋና ሀላፊ ነገር ግን እርዳታው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች እየደረሰ አይደለም ብለዋል፡፡ ሁለቱ ተፋላሚዎች የእርዳታ መጋዘኖችን በመቆጣጠር ምግብን እንደ ጦር መሳሪያነት እየተጠቀሙበት ሲሉ ከሰዋል፡፡

በተጨማሪም የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የእርዳታ እህሎችን ፣ የቁም እንስሳትን እንዲሁም የጥራጥሬ እህሎች ዘረፋ ላይ መሰማራቱን ነው የገለጹት፡፡ 

የሱዳን ጦር በበኩሉ ከቻድ ወደ ሱዳን የሚወስደውን በዳርፉር ግዛት ብቸኛ የእርዳታ መተላለፊያ ሀገር አቋራጭ መንገድ በመዝጋት ለእርዳታ ድርጅቶች ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አድርጓል፡፡ በዚህ የተነሳም ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከጦርነቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በረሀብ እየሞቱ ይገኛሉ፡፡

 በተባበሩት መንስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ የረሀብ አደጋው በከፋባቸው ዳርፉር እና ኮርዶፋን እስከ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡ 

በሱዳን ያለው ስጋት ከ1977ቱ የኢትዮጵያ ረሀብ በኋላ ምድር የምታስተናግደው አስከፊው ሰበአዊ ቀውስ ሊሆን ይችላል፡፡ 

በሀገሪቱ ለዜጎች እርዳታ ለማድረስ ካለው ፈተና ባለፈ በቂ ድጋፎችን ለማሰራጨት ያለው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ሌላው እራስ ምታት ነው።

 በዩክሬን እና ጋዛ ጦርነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው አለም የሱዳንን ጉዳይ ቸል ያለው ይመስላል፣ ሁለቱ ጦርነቶች የአለም አቀፍ ጂኦፖለቲክስ መፋተጊያ በመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረትን ሲያገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን ያስተዋለው ጥቂት ነው፡፡ 

ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ላይ የተቀሰቀሰው የሁለቱ ጀነራሎች ጦርነት እስካሁን የ14ሺ ንጹሀን ሱዳናዊያንን ህይወት ሲቀጥፍ 10 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

By Al Ain Amharic News

አል ዐይን ኒውስ ሁሉን አቀፍ ሽፋን የሚሰጥ እና የዓለም ክስተቶችን በወቅቱና በጊዜው ለተከታዮቹ ያቀርባል፡፡

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው