በጸጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ሌሎች 40 የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጠት ሂደት አልተከናወነም   

በሙሉጌታ በላይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት ሊካሄድ የነበረውን የ“ቀሪ ምርጫ” ሂደት ለነገ ማስተላለፉን አስታወቀ። ቦርዱ “አንሻ ገብርኤል እና ገንገን” በተባሉ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫውን ማካሄድ ያልቻለው የምርጫ ቁሳቁሶች በጊዜ ባለመድረሳቸው መሆኑን ገልጿል።

ብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ሂደቱ ሳይከናወን በቀረባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ዛሬ እሁድ ሰኔ 16፤ 2016 ሲካሄድ ውሏል። የዛሬው የቦርዱ መርሃ ግብር፤ ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንባቸው ቦታዎችንም ያካተተ ነበር።

ምርጫ ቦርድ “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ” ለማድረግ አቅዶ የነበረው በ1,258 የምርጫ ጣቢያዎች ቢሆንም፤ የዛሬው የድምጽ መስጠት ሂደት የተከናወነው በ1,218 ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች፤ የጽምጽ መስጠት ሂደቱ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ የቀጠለ እንደነበርም ተገልጿል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ቦርዱ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የጊዜ ማራዘሚያ ያደረገው፤ የድምጽ መስጠት ሂደቱ “ዘግይቶ  በመጀመሩ” መሆኑን አስታውቋል። በዚሁ ክልል በሚገኘው ገንገን ምርጫ ጣቢያ፤ የምርጫ ቁሳቁሶች የተጓጓዙት ዛሬ ጠዋት በመሆኑ የድምጽ መስጠት ሂደቱን “በሰዓቱ ማከናወን” እንዳልተቻለ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስረድተዋል።

እንደዚህ ምርጫ ጣቢያ ተመሳሳይ የቁሳቁስ መዘግየት ባጋጠመው አንሻ ገብርኤል ምርጫ ጣቢያ፤ በነገው ዕለት የድምጽ መስጠቱ ሂደት እንደሚከናወን ሜላተወርቅ አመልክተዋል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ ሌሎች 40 የምርጫ ጣቢያዎች፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት የዛሬውን ምርጫ ሳያካሄድ ቀርቷል።

ምርጫ ቦርድ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቦርዱ፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጣ “የጸጥታ ሁኔታ ክትትል ቡድን”፤ ምርጫ በሚደረግባቸው ክልሎች ያደረገውን “ዳሰሳ” መሰረት በማድረግ መሆኑን በትላንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የጸጥታ ሁኔታ ክትትል ቡድኑ፤ ምርጫ ሊደረግባቸው “የሚችሉ እና የማይችሉ” በሚል አካባቢዎችን “በቀይ፣ በአረንጓዴ እና በቢጫ” ፈርጇል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

“በቀይ በመፈረጃቸው” ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደባቸው 40 የምርጫ ጣቢያዎች፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቡለን፣ በድባጤ እና ማንዱራ ወረዳዎች የሚገኙ ናቸው።

የእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች “ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?” የሚለውን፤ ቦርዱ “ተነጋግሮ፤ ውሳኔ ካሳለፈ” በኋላ እንደሚያሳውቅ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በትላንቱ መግለጫቸው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

By Ethiopia Insider

Ethiopia Insider is your news, analysis, features and entertainment website.