አዲስ አበባ፡- መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ፣ የመሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባትና በጀት በመመደብ የሰላም ስምምነትን ተግባራዊ በማድረግ ብዙ ርቀት መጓዙን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ፓርቲ አባል ኮማንደር ገብረመስቀል ገብረሚካኤል ገለጹ።

የትዴፓ ፓርቲ አባል ኮማንደር ገብረመስቀል ገብረሚካኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤መንግሥት የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ርቀት ተጉዟል። በትግራይ ክልል የሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ፣ የመሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት፣ በጀት በመመደብ፣ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግና ሌሎች ሥራዎችን በማከናወን የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን ብዙ ረቀት ተጉዟል።

በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረገውን የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ተከትሎ መንግሥት ብዙ አወንታዊ ሥራዎች በክልሉ ሠርቷል ያሉት ኮማንደር ገብረመስቀል፤አሁንም መንግሥት ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኘ ገልጸዋል።

እንደ ኮማንደሩ አገላለጽ፤የፌዴራል መንግሥት በተለይ ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ከሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ጋር ተያይዞ እየሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ፣ቴሌኮም እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲሟሉ አድርጓል። የጤና ተቋማት ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉም የሚመሰገን ነው።

ሥራቸውን አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።በዚህም የተነሳ ብዙ ፋብሪካዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን አውስተው፤መንግሥት የሰላም አስፈላጊነትን በማመኑ ብዙ ወጪ በማውጣት በርካታ መሠረተ ልማቶችን ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።በጥቅሉም በርካታ አወንታዊ ሥራዎችም ሠርቷል ነው ያሉት ።

መንግሥት የሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ይሁን እንጂ እርዳታ ከሚያስፈልገው የሰው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ውስንነት ቢኖርም ሕዝቡ እርስ በርስ መደጋገፍ ክፍተቱን መሸፈን እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

የሰላም ስምምነቱ ካስቀመጠው ግዴታ ባለፈ የፌዴራል መንግሥት መተማመን ለመፍጠር እና ሰላም ለማጠናከር ያስፈልጋሉ ያላቸውን ፖለቲካዊ እርምጃዎች በተከታታይ መውሰዱን ጠቅሰው፤ ሰብአዊ ድጋፍም ያለ ምንም እንቅፋት ወደ ክልሉ የሚደርስበት ሁኔታ መፍጠሩን አስገንዝበዋል።

እንደ ኮማንደር ገብረመስቀል በክልሉ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ብዙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ አስችሏል።የስምምቱ አተገባበር የተወሰነ ክፍተት ቢኖርበትም በፌዴራል መንግሥት በኩል ስምምነቱን ለመፈጸም የተደረጉ ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው።

የሰላም ስምምነቱ ከትግራይ ሕዝብ ባሻገር ለኢትዮጵያ ሕዝብም ተጨባጭ ጥቅም ማስገኘቱን አመልክተው፤በስምምነቱ መሠረት ዘላቂ ሰላም እንዲፀና የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት በቆራጥነት ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ትጥቅ አለማስፈታቸውና ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት አለመመለሳቸው የስምምነቱ ክፍተቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የሰው ልጆች ህይወት መቀጠፍንና የንብረት ውድመትን የታደገ ነው ያሉት ኮማንደሩ፤በስቃይ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ ኮማንደሩ አገላለጽ፤ስምምነቱ ለኢትዮጵያም ይሁን ለአፍሪካ ብዙ ትምህርት ያስገኘ ነው። ምክንያቱም በቀላሉ መተማመንን መፍጠር ከባድ ነው።በተለይ ፖለቲካዊ ችግርን በንግግር የመፍታት ባህል እንዲዳብር በር ከፋች ነው፤ይህ ለሌሎች ታጣቂ ኃይሎችም ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ነው።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም መደረጉ የሚታወስ ነው።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

By Ethiopia Press Agency

Ethiopian Press Agency is a public media enterprise operating in Ethiopia.

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው